የክቡር የአቶ ጀማል አባሶ መልዕክት
ኢትዮጵያ ከ118 ሚሊዮን በላይ ህዝቦችን በመያዝ ከናይጀሪያ በመቀጠል በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ሀገር ስትሆን በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ሀገራችን ዝቅተኛ የተሸከርካሪ ቁጥር ካላቸው ሀገሮች ውስጥ አንዷ ብትሆንም በትራፊክ አደጋ ብዙ ሞትንና የንብረት ውድመትን ታስተናግዳለች፡፡
ለአንድ ሃገር ሁለንተናዊ ዕድገት ዘመናዊ፣ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት መስፋፋት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ጉዳዮች ውስጥ የመንገድ ትራፊክ አደጋ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ አደጋው የበርካታ ዜጎችን ህይወት በመቅጠፍና አካል በማጉደል ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት በማድረስ ላይ ነው።
እንደ አለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.ኤ.አ የ2018 ዓመት ሪፖርት መሰረት በትራፊክ አደጋ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአማካኝ 1.35 ሚሊዮን ሰዎች በየዓመቱ በትራፊክ ግጭት የሚሞቱ ሲሆን ከ20 እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱት ደግሞ ለሞት የማይዳርግ ጉዳት እንዲሁም ከ600 ቢሊዮን ዶላር በላይ የንብረት ውድመት ይደርሳል፡፡ በተለይም ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 29 እድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች ዋነኛ የትራፊክ አደጋ መንስዔዎች ናቸው፡፡
በሀገራችን ከ2010 እስከ 2014 በአማከኝ ከ4 ሺ በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ሲሆን ከ10 ሺ በላይ የሚደርሱት ደግሞ ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንዲሁም ከ13 ቢሊዮን በላይ የንብረት ውድመት ይደርሳል፡፡ በአብዛኛው የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎችም ከ18 እስከ 50 ዓመት ያሉ አምራች ኃሎችን ይጎዳል፡፡
የመንገድ ትራፊክ አደጋ ከ 90 በመቶ በላይ የሚከሰተው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እነዚህ ሀገራት በዓለም ከተመዘገቡ ተሸከርካሪዎች ከ60 በመቶ ያነሰ ቁጥር ይይዛሉ፡፡
ስለሆነም የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት በደንብ ቁጥር 493/2014 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቋቁሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከልና የተሸከርካሪ አደጋ ተጎጂዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቀነስ የማስተባበር፣ የመምራትና የመደገፍ ኃላፊነትንና ተግባር ተሰጥቶት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በዚህም መሰረት ተቋማችን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽና ሥራ ላይ በማዋል የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም በማሳደግ፣ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማረጋገጥ የተቀናጀ ፣የተቀላጠፈ ግልጽ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ለዜጎች ከቅድመ ትራፊክ አደጋ እስከ ድህረ ትራፊክ አደጋ ምላሽ በመስጠት ዜጎች ከትራፊክ አደጋ እንዲጠበቁ የማድረግ ተልዕኮውን ለማስፈጸም ተግባራትን ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡
ማንኛውም ሰው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ምክንያት ለሞት ወይም ለከፋ የአካል ጉዳት ገንዘባቸውን ሆነ ህይወታቸውን ሊከፍል አይገባም፡፡ የመንገድ ደህንነት ችግር የሁሉንም የሰው ልጅ እና አካላት የሚመለከት ነው፡፡ በመሆኑም ችግሩንም ለመቅረፍ የሁሉም የሰው ልጆችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ተሳትፎ ወሳኝነትና ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
የመንገድ ትራንስፖርት ስርዓት ዘርጊዎች እና አስተዳዳሪዎች፣ ሚዲያና አስተማሪዎች፣ የፈጠራ ሰዎች፤ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች፣ የመንገድ ተጠቃሚዎች፣ፖለቲከኞች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይዎት ከትራፊክ አደጋ ለመታደግ የራሳቸውን ሚና ለመወጣት ኃላፊነት አለባቸው፡፡
የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት መ/ቤቱ ብሄራዊ የ10 ዓመቱን መሪ ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርፆ በ10 ሺ ተሽከርካሪ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ የሞት ቁጥር ወደ 10ሰው ለማድረስ ስራዎችንእየሰራ ይገኛል፡፡
ከመንገድ ትራፊክ አደጋ የተጠበቀ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ከክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ጋር የተጀመረውን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክረን በማስቀጠል እንዲሁም የመንገድ ደህንነት ጉዳይ የፓርላማ አባላት፣ የከፍተኛ ፖለቲከኞች አጀንዳ እንዲሆን እና በልዩ ትኩረት እንዲመራ በማድረግ በተጨባጭ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በበቂ ሁኔታ በማሳተፍ የችግሩ የመፍትሄ አካል እንዲሆን ለማስቻል እተሰራ ይገኛል፡፡
ስለዚህ በሀገራችን ያለውን አስከፊ የመንገድ ትራፊክ አደጋን በጋራና በተቀናጀ መልኩ በመንቀሳቀስ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ብልፅግናን እውን በማድረግ በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባ ህብረተሰብን ለመፍጠር በጋራ እንድንሰራ ጥሪ አስተላልፋለሁ፡፡
የወ/ሮ ፈቲያ ደድገባ መልዕክት
ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ እና በሁለንተናዊ ብልፅግና የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ የመንገድ ትራንሰፖርት አገልግሎት ዘርፍ የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ የሀገሪቱ የገቢና ወጪ እቃዎች ዝውውር ከ95% በላይ እና ከ97% በላይ የመንገደኞች እንቅስቃሴ በአማካይነት የሚሸፍን መሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ስለሆነም መንግስት፣ የባለድርሻ አካላት እና ተጠቃሚው ማህበረሰብ በተቀናጀ እና በወጥነት አሰራር ላይ ትኩረት በመስጠት የአገልግሎት ዘርፉን ቀልጣፋና ውጤታማ፤ ደህንነቱንና ምቾቱን የተጠበቀ፤ ቀጣይነቱን እና ተአማኒነት እንዲኖረው ማድረግ ወሳኛ እና ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡
በሀገራችን በመንገድ ትራፊክ አደጋ ከ2010ዓ.ም -2014ዓ.ም በአማካይ በየዓመቱ ከ4,000 በላይ የሰዎች ህልፈተ ህይወት፣ ለከባድና ቀላል አካል ጉዳት እና በሚሊዮን የሚገመት ንብረቶች በመውደም ላይ የገኛል፡፡
ይህንን አስከፊ አደጋ ለመቀነስ የተለያዩ አካላት ሀላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን ሀላፊነት ከተሰጣቸው ተቋማት አንዱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 493/2014 እንዲቋቋም የተደረገው የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት መ/ቤት ነው፡፡
መ/ቤቱ የተሰጠውን ሀላፊነት ለመወጣት የ10 ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድን አዘጋጅቶ እና አደረጃጀትን ፈጥሮ የመንገድ ደህንነት ፕሮግራሞችን(የመንገድ ደኅንነት ማኔጅመንት ሥርዓት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ፍጥነት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ተሸከርካሪ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ ተጠቃሚ እና ድህረ አደጋ ምላሽ) በመተግበር የመንገድ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን በማድረግን ማንም ሰዉ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሞት ወይም ከባድ የአካል ጉዳት እንዳያስተናግድ ለማስቻል በትራፊክ አደጋ የሚደርሰዉን ሞት እ.ኤ.አ በ2021 ካለበት ደረጃ 2030 ላይ በ50% መቀነስ ግብ አስቀምጦ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ስለሆነም ይህን ግብ ለማሳካት መ/ቤቱ በአንድ ዓመት ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ሀገር አቀፍ የተጠናከረ የህግ ማስከበር፣ ለተጎጂዎች የህክምናና የካሳ ከፍያዎችን የመፈፀም፣ አዳዲስ ህጎችን አማውጣት እና ነበር ህጎችን የማሻሻል፤ አቅም ግንባታ እና ቅንጅታዊ አሰራሮች እንዲሁም ዘመናዊ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን የማልማት ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በቀጣይ የተጀመሩ ስራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ በማስቀጠል የተቀረፀውን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ በጀት፣ ዕውቀት እና የህዝብና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ድጋፍ አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳዮች ሲሆኑ እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮችን አስተባብሮና አቀናጅቶ በቁርጠኝነት የመምራት ሀላፊነቶች የመ/ቤቱ አመራሩና ሰራተኛው ሀላፊነቶች ናቸው፡፡
ስለዚህ በሀገራችን ያለውን የመንገድ ትራፊክ አደጋ በመከላከል ማንም ሰዉ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሞት ወይም ከባድ የአካል ጉዳት እንዳይደርስበት በሚሰሩ ስራዎች ላይ ህዝቡ፣ የሚመለከታችሁ ባለድርሻ አካላቶች፣ የመ/ቤቱ የስራ ሀላፊዎች እና ሰራተኞች የበኩላችሁን አስተዋፆ እንድትወጡ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡