በአገራችን አስር ገዳይ የጤና ችግሮች ከሚባሉት ውስጥ የሚገኘው በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት የሚከሰት ሞትን ለመከላከል ሁሉም በጋራ መስራት ያስፈልጋል ።- የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ዱግማ

24 Jun 2023

በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሽከርካሪ ብዛት እየጨመረ እንደሆነ የተናገሩት የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ደረጀ፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፓርት እንደሚያመላክተው እድሜያቸው ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ ዘጠኝ ያሉ ታዳጊዎች በብዛት በትራፊክ አደጋ እንደሚሞቱ ገልፀው ፣የትራፊክ ደህንነት ጉዳይ በአገራችን ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላክተዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የድንገተኛ አደጋ ህክምና ዓመታዊ አፈፃፀምን ከመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት ጋር በመሆን የገመገመ ሲሆን፤ የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች እና ምላሹ በተወሰነ ሴክተር መ/ቤት ብቻ የሚመለስ ሳይሆን የሁላችንንም የነቃ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ዶክተር ደረጀ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ዶክተር ደረጀ አክለውም አስቀድሞ አደጋው እንዳይደርስ መከላከል ፣ ከደረሰ ደግሞ አፋጣኝ ህክምና በመስጠት የጉዳቱን መጠን መቆጣጠር ካልተቻለ አምራች የሆነውን የነገ አገር ተረካቢ ዜጋ በማሳጣት ከቁጥር በዘለለ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ጫና ያሳድራል ብለዋል።

የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ጀማል አባሶ የጤና ሚኒስቴር በተሽከርካሪ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች ግንባር ቀደም ባለድርሻ ሆኖ እየሰራ እንደሆነ ገልፀው፣ ፓሊስ እና ጤና ተስማምተው በመናበብ አገልግሎቱን የበለጠ ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በተሽከርካሪ አደጋ የሶስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2005 አንቀፅ 27 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ማንኛውም ዜጋ በተሽከርካሪ ምክንያት ጉዳት ከደረሰበት እስከ ሁለት ሺ ብር ድረስ በማንኛውም ጤና ተቋም ነፃ የህክምና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው ህጉ ቢደነግግም የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እየሆነ እንዳልሆነ እሚያመላክቱ መረጃዎች መኖራቸውን አቶ ጀማል ተናግረዋል።

ከፌደራል እና ከክልል የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተው የ2015 ዓ.ም. የአፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በቀጣይ በ2016 ዓ.ም.በጀት ዓመት ለማሻሻል በቁርጠኝነት ለመስራት ቃል ገብተው በተጨማሪም አሁን ላይ በተግባር ያለው የድንገተኛ አደጋ ህክምና እስከ ሁለት ሺ ብር የሚለው በቂ ስላልሆነ በቀጣይ ወቅቱን ያገናዘበ ለማድረግ እየተጠና መሆኑ ተገልጿል።

ምንጭ ፣የጤና ሚኒስቴር